በስተቀኝና በስተግራዬ ካፌው ግድግዳ ላይ መስኮት የመሰሉ ትናንሽ ሽራዎች ተሰቅለውበታል፡፡ ፊት ለፊቴ ከእኔ አንድ ወንበርና ጠረጴዛ እርቆ ኣንዱ ግድግዳ ከላይእስከታች በአንድ ሥዕል ተሸፍኗል፡፡ ሥዕሉ የንፋስስልክ አዕዋፍ ይላል፡፡ በአንድ ሥዕል መሽፈኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሥዕሉ ላይ ያሉት ወፎች ብቻ ናቸው:: እዛ ሥዕል ላይ ጎልታ ከምትታየው አንዷ ወፍ በስተቀር የቀሩት አምሳ ወይም መቶ የሚደርሱት መጠናቸው እኩል ነው:: ሥዕሉ ሶስት ቀለማት ብቻ አሉት፡፡ አረንጓዴ መስክ፣ የሰማይ ሰማያዊና ጥቋቁር አዕዋፍ ሰማዩ ላይ ሲበሩ። ከሁሉ የምትተልቅ አንዲት ወፍ ሥዕሉ መሃል ላይአለች፡፡ ሁለመናዋ ጥቁር ይሆንና ሆድዋ ብቻ የዕንቁላል ቅርፅ ያለው ነጭ ነው:: ከሥዕሉ በስተቀኝ ታች ላይ
ወፌ ብረሪ ብረሪ
ወፌ ብረሪ ብረሪ
ይላል። የሰአሊው ስም ነው መሰለኝ ከጽሑፉ ስር “ወዕ’ የሚል ተጽፏል፡፡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥዕል አጠገብ ነበርኩ፡፡ ሁሉ ነገሩ ደስ እያለ የሚያስፈራ ነው:: ምናልባት ትርጉሙ ስላልገባኝ ይሆናል። እሱ ላይ ሳፈጥ ዕፀሕይወት ሁለት ቡናና አንድ ኬክ ይዛ መጣች፡፡
የስንብት ቀለማት